የሂልተን ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ አፈና !
" ከደህንነት ተደውሎ ስለተነገረን አሁን መግለጫ መስጠት አትችሉም "
በዛሬው ዕለት ለሁለተኛ ጊዜ ሰናይ መልቲ ሚዲያ ምስረታና የአክሲዮን ሽያጭ፤ ይፋዊ መግለጫ መንግስታዊ አፈና በድጋሚ ተካሂዶበታል ።
ለአዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል በቀን 27/ግንቦት/2011 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ ፤ "ጌት አማካሪዎች" የንግድና ኢንቨስትመንት ማማከር ድርጅት፤ የሰናይ ቲቪ ምስረታ እና አክሲዮን ድርሻ ሽያጭን በተመለከተ ፤ለግንቦት 30/2011 ዓ.ም ከጠዋቱ 4 እስከ 6 ሰዓት ለሚደረገው ጋዜጣዊ መግለጫ የአዳራሽ ኪራይ የተጠየቀ ሲሆን ፤
ሂልተን ሆቴል በደብዳቤ ለቀረበለት ጥያቄ ግንቦት 28 ቀን 2011 ዓ.ም አወንታዊ ምላሽ በደብዳቤ በመግለጽ፣ ክፍያ እንዲፈጸም በጠየቀው መሰረት በዚው ዕለት 12995 ብር (አስራ ሁለት ሺህ ዘጠኝ መቶ ዘጠና አምስት ብር ) ክፍያ ተፈጽሟል ።
ይሁን እንጂ በተገባው ህጋዊ ውል መሰረት፣ በዛሬው ዕለት ጥሪ የተደረገላቸው ጋዜጠኞች እና ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት የተገኙ የሰናይ መልቲ ሚዲያ መስራቾች ፣በቦታው ቢገኙም የተሳበው መግለጫ መስጠት አልተቻለም ።
ይህን ጉዳይ በተመለከተ የሆቴሉ የሽያጭ ክፍል እረዳት ስራ አስኪያጅ አቶ አንተነህ ሰርጸወልድ " ከሚመለከተው ክፍል ፍቃድ ካላመጡ መግለጫ እንዳይሰጡ" በማለት ከደህንነት ተደውሎ ስለተነገረን አሁን መግለጫ መስጠት አትችሉም ብሏል ። ለእኚህ ስራ አስኪያጅ የሰናይ መልቲ ሚዲያ መስራቾች "የሚመለከተው" አካል ማነው ?ይህን ማድረግ ከእኛ አይጠበቅም !ዝግጅታችን አጠናቀናል፣ ህጋዊ ውል ፈጽመናል ፣ መግለጫ እንድንሰጥ ወደ አዳራሹ እንድንገባ በሩ ይከፈትልን ፤ በማለት ጥያቄ ያቀረቡ ቢሆንም፤ አቶ አንተነህ የሆቴሉን ጥበቃዎችን በመጥራት የአዳራሹ በር በማዘጋት ፣" ይሄ ከእኔ አቅም በላይ ስለሆነ ፤ ጊቢውን ለቃችሁ ውጡልኝ " ብለዋል ።
የሰናይ መልቲ ሚዲያ መስራቾች ይህ'ን መንግስታዊ የሚዲያ አፈና ፣እዛው በመረጃና በማስረጃ በሆቴሉ ቅጥር ግቢ ለተገኙ የሚዲያ ተቋማት በመግለጽ ፣ ግቢውን ለቀው ወጥተዋል ።
ከላይ ለተዘረዘሩት የውል ስምምነት ማስረጃ ከዚህ ጽሁፍ ጋር ተያይዟል ፣እኔ'ም በቦታው ስለነበርኩ እማኝነቴን እገልፃለው።
ድል ለእውነተኛ ዴሞክራሲ !!!
Comments
Post a Comment