መረጃ  (Ethio 360 Media)

የአዲስ አበባ ህዝብ ሰላማዊ ሰልፎችን ለማድረግም ሆነ ሕዝባዊ ስብሰባዎችን እንዳያደርግ ማዕቀብ ተጥሎበታል።--ጋዜጠኛና የመብት ተማጓች እስክንድር ነጋ
(ኢትዮ 360 - ሐምሌ 3/2011) የአዲስ አበባ ህዝብ ሰላማዊ ሰልፎችን ለማድረግም ሆነ ሕዝባዊ ስብሰባዎችን እንዳያደርግ ማዕቀብ ተጥሎበታል ሲል የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት ባልደራስ አስታወቀ።
ምክር ቤቱ ይህን ያለው ዛሬ ባልታወቁ ሰዎች እንዲቋረጥ በተደረገው መግለጫው ላይ ነው።
የሕሊና እስረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ይፈቱ በሚል ባወጣው መግለጫው ዛሬ ላይ የጭቆና ቀንበር ውስጥ ወድቀናል፣በተለይ የአዲስ አበባ ሕዝብ ሰላማዊ ሰልፍም ሆነ ሕዝባዊ ስብሰባዎችን እንዳያደርግ ማዕቀብ ተጥሎበታል ብሏል በመግለጫው ላይ የተገኘው የምክር ቤቱ ሰብሳቢ እስክንድር ነጋ።
ኢትዮጵያ ዛሬ የሕሊና እስረኞች ያሉባት ሃገር ሆናለች ያለው የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ እስክንድር ነጋ የሕወሃት አገዛዝ ከተገረሰሰ ከአንድ አመት በኋላ በርካቶች በሕሊና እስረኝነት ወደ እስር እንዲጋዙ ተደርጓል።
የባላደራው ምክር ቤት ዋና ጸሃፊን ኤልያስ ገብሩና የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊውን ስንታየሁ ቸኮልን ጨምሮ በርካቶች ለእስር ተዳርገዋል።
ከእነዚህ እስረኞች በአብዛኞቹ ላይ ፖሊስ በባህርዳር ከተፈጸመው ችግር ጋር ንክኪ አላቸው በሚል በኢትዮጵያ ሕዝብ፣በአዲሱ አመራርም ሆነ በአለም አቀፉ ማህበረሰብ በተወገዘው የሽብር ህግ ክስ መስርቶባቸው በእስር ላይ ይገኛሉ።
በባህር ዳርም ሆነ በአዲስ አበባ የተከሰቱት ችግሮች መጀመሪያቸውም ሆነ መጨረሻቸው ኢሕአዴግ ውስጥ የተፈጠረ ልዩነት መሆኑ እየታወቀ በባላደራው አባላት ላይም ሆነ በሌሎች ላይ እየተወሰደ ያለው የእስር ርምጃ አሳዛኝ ነው፣አንቀበለውምም ብሏል።
እንዲህ አይነቱ አካሄድ ለሃገራችን ከፍተኛ የሆነ የኋላዮሽ ጉዞ ነው ሲል በመግለጫው አስፍሯል።
በንጹሃን ዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለውን እንዲህ አይነቱን ድርጊት የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ከጎን ቆሞ እነዚህ የህሊና እስረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ ግፊት እንዲያደርግ ጥሪውን አስተላልፏል።
ጋዜጠኛና የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ እስክንድር ነጋ በመግላጫው ላይ እንዳለው ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ በተለየ ይህንን ጥሪ የምናቀርበው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነው ብሏል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ለነዚህ ዜጎች ድምጹን የማያሰማ ከሆነ የእስር ጊዜያቸው ሊራዘምና እነሱም በእስር ቤት እንዲማቅቁ ሆኑ ማለት ነው።-ስለዚህ ወሳኙ የኢትዮጵያ ህዝብ ነው ብሏል።
በዚህ ረገድ በውጭ ያለው ማህበረሰብም ትልቅ ሃላፊነት አለበት፣በጭቆና ስር ላሉ ወገኖቹ ሊጮህ ይገባል ብሏል።
የመብት ተሟጋቹ እስክንድር እንደሚለው ከሆነ አሁን ላይ በሃገር ውስጥ ድምጽን ማሰማት እንዳይቻል አፈና አለ።ስለዚህ ይህንን ማድረግ የሚችለው በውጭ በነጻነት ድምጹን ማሰማት የሚችለው ኢትዮጵያዊ ነው።
በተለይ በዋሽንግተን ያሉ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ ኤምባሲና በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ፊት ለፊት በመሄድ በኢትዮጵያ የሕሊና እስረኞች መፈጠራቸውን፣የዲሞክራሲ መብቶች እየተደፈጠጡ መሆኑን ድምጻቸውን ከፍ በማድረግ ማሰማት አለባቸው ብሏል።
በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ እንደከዚህ በፊቱ ሁሉ የኢትዮጵያ ህዝብ ልሳን፣የኢትዮጵያ ህዝብ ህሊና ሆኖ እንድቆምም ጥሪ አስተላልፏል።
ወደ አዳራሹ መግለጫ ለመስጠት ሲገባ ሲቪል የለበሰ ፖሊስ እንዳይገባ ከልክሎት እንደነበር የተናገረው እስክንድር ለዘገባ ወደ አዳራሹ ሊገቡ የነበሩ ጋዜጠኞችም ወደ አዳራሽ እንዳይገቡ ወከባ ሲፈጸምባቸው እንደነበርም ተናግሯል።
በመግለጫው ላይ ከጋዜጠኞች ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ በነበረበት ወቅትም ማንነታቸው ያልታወቀ ወጣቶች በፈጠሩት ረብሻ ምክንያት ጥያቄና መልሱ ሳይካሄድ መቅረቱ ተገልጿል።
በአካባቢው የነበሩ የአይን እማኞች እንደሚሉት ከሆነ በአዳራሹ ገብተው ረብሻ ሲፈጥሩ የነበሩት ወጣቶች አዲሶችና ከዚህ በፊት በነበሩት መግለጫዎች ላይ ያልታዩ ናቸው።
እንደ አይን እማኞቹ ከሆነ ችግሩን ሲፈጥሩ የነበሩት ወጣቶች ከአዳራሹ ከወጡ በኋላ የተሽከርካሪና የሰው መተላለፊያ ዘግተው በፖሊስ ጥበቃ እየተደረገላቸው መግለጫ ይሰጡ እንደነበር ተናረዋል።

Comments

Popular posts from this blog

Addis standard’s exclusive interview with Ana Gomes