የዘረኞች ባንዲራ ቤቱ ሙዚየም ነው! (ታሪኩ አባዳማ)

በዩኤስ አሜሪካ የግንጠላ ታሪክ ውስጥ ጎልቶ የሚታወቀው የደቡብ ክፍለ ግዛት ባሪያ አሳዳሪ ነጮች እንቅስቃሴ ነፀብራቅ የነበረው ባንዲራ እንዳይወጣ ሆኖ ወረደ። የደቡብ ካሮላይና ግዛት ምክር ቤት በወሰነው መሰረት ለምዕተ ዓመት ሲውለበለብ የነበረው የኮንፌዴሬት ዘረኛ ባንዲራ በቄንጠኛ ስርዓት ከተሰቀለበት ወርዶ ወደ ሙዚየም ተልኳል – የዘረኞቹ ባንዲራ ዘላለማዊ ቦታውን ተጎኗፅፏል። የ19ኛው ክፍለ ዘመን ባሪያ አሳዳሪ ዘረኛ ግፈኞች የሰቀሉት ባንዲራ ዛሬ ቢወርድም በራሳችን አገር በ21ኛው ምዕተ ዓመት በየመንደሩ ተፈብርከው የተሰቀሉ መርዝ የሚነሰንሱ ዘረኛ ባንዲራዎች ደግሞ ተራቸውን እየጠበቁ ነው።Ethiopian racist flag
የደቡብ ካሮላይና ተገንጣዮችን ከኛ አገር ተገንጣዮች የሚለያቸው ነገር ቢኖር የቆዳ ቀለማቸው ብቻ ነው። እርግጥ ነው እኛ አገር ዘረኛ ተገንጣዮች የመንግስት ስልጣን ለመጨበጥ እና ያሻቸውን አስገንጥለው የቀረውንም በዘር ግንድ ከፋፍለው እያንዳንዱ ባንዲራ እንዲነሰንስ ብቻ ሳይሆን አንዱ ሌላውን ዘር ላይ በተመረኮዘ ጥላቻ እና ጥርጣሬ ተፋጦ እንዲቀመጥ ማድረግ ችለዋል – የደቡብ ካሮላይና ዘረኞች ግን የግንጠላ አላማቸውን ማሳካት አልበቁም። በተባበረው አሜሪካ አንድነት ሀይል ክንድ ተደቁሰው የግንጠላ ባንዲራቸውን ግን ታቅፈው ነበር የቆዩት። ዘረኝነት በደም ሲወርድ ሲወራረድ መጥቶ ያንን ጦሰኛ ባንዲራ ከለላ ያደረገ ነጭ ዘረኛ ዘንድሮ እንኳ የዘጠኝ ጥቁሮችን ደም ከደጀሰላም በግፍ አፍሷል – ባንዲራው ሰላምን እና ፍቅርን ሳይሆን ጥላቻ እና ቂም ሲነሰንስ መኖሩን የተረዱ የዛሬው ዘመን አሜሪካውያን ባንዲራውን ከከረፋ ፀያፍ ታሪኩ ጋር ቦታህ ሙዚየም ነው ብለውታል። የፈጀውን ጊዜ ይፈጃታል እንጂ ዘረኞች የሰቀሉት ባንዲራ የትም ይሁን የት ከገፀ-ምድር ተፍቆ አንድ ቀን ወደ ሙዚየም መግባቱ አይቀሬ መሆኑ የተረጋገጠበት አጋጣሚ ነው። ተተኪው ትውልድ ውደ ሁዋላ ዞር ብሎ ሲያይ ማን በትክክለኛው የታሪክ ጎዳና ላይ እንደቆመ እንዲህ ይመሰክራል።
ብሔራዊ ሰንደቅ አላማ አንድ ሉአላዊ አገር የሚታወቅበት የሚገለፅበት መለያ መታወቂያ አምድ ነው። ሁሉም ዜጎች ራሳቸውን ከብሔራዊ ሰንደቅ አላማ ጋር የሚያስተሳስሩበት ታሪካዊ አጋጣሚ አለ። ባንዲራችን የማይደለዝ የማይሰረዝ ነው ስንል ባንዲራውን ተሸክመው ያገራችንን ነፃነት ፣ አንዲት አትዮጵያ ብለው ዳር ድንበር እና ክብር ሲጠብቁ ፣ ሲያስከብሩ ለነበሩ ጀግኖች ያለንን ክብር ማረጋገጣችን ነው።
ከአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ በስተጀርባ የሚታየኝ ባልቻ አባነብሶ መድፉን አነጣጥሮ የጣሊያንን ወራሪ ጦር ሰፈር ሲያነውጥ ነው ፣ ከባንዲራው በስተጀርባ የሚታየኝ እምቢኝ ለአገሬ ብሎ ማይጨው ላይ በመርዝ ጪስ የተጠበሰው ዜጋ ነው – ከባንዲራው በስተጀርባ የሚታየኝ የዚያድ ባሬን ወረራ ለመመከት ሳያሰልስ ቆርጦ የተመመው ከሁሉም የአገሪቱ ክልል የፈለቀው ጀግና ሰራዊት ነው ፣ ከባንዲራው በስተጀርባ የሚታየኝ መሬት ላራሹ ብሎ ፍትሀዊ አስተዳደር እንዲሰፍን የታገለው ትውልድ ነው ፣ ከባንዲራው በስተጀርባ የሚታየኝ የዕውቀት ብልጭታን ለመፈንጠቅ በመላ ገጠር ኢትዮጵያ የዘመተው የእድገት በህብረት ዘማች ነው… እኔ ከባንዲራው በስተጀርባ ደርግም አፄውም አይታዩኝም – አበበ ቢቂላ በሉት የጥቁር አንበሳው ጦር መሪ ኮለኔል በላይ ገብረአብ ወይንም በላይነህ ዴንሳሞ ባንዲራችንን በኩራት ከፍ አድርገው ሲያውለበልቡ የነበረው የአንድነታችን እና የነፃነት ክብራችን መግለጫ ስለሆነ ብቻ ነው። ከብሔራዊ ባንዲራ በስተጀርባ ያለው ህዝብ እና አገር ናቸው። ባንዲራ ለድሀው ሆነ ሀብታሙ ፣ ለገዢው ሆነ ተገዢው ፣ ለገበሬው ሆነ ወዛደሩ ፣ ለተማረው ሆነ ለመይሙ ፣ ጠግቦ ለሚያድረው ሆነ ለተራበው ሳይቀር ለሁሉም እኩል ትርጉም ሊኖረው ይገባል። አለበለዚያ ካንድ ያገሪቱ ጫፍ የተነሳ የጦር አበጋዝ እሱ የመሰለውን ጨርቅ ጠቃቅሞ በብረት ያስገበረውን ሁሉ ይሔ ባንዲራህ ነው ቢል ውሎ አድሮ የሀይል ሚዛን ያጋደለ ጊዜ ውጤቱ አያምርም…
ደቡብ ካሮላይና ትመስክር!!
በኢትዮጵያ ብቻ ዘረኛ የጦር አበጋዞች የበላይነት ተቀዳጅተው ዘረኝነትን በግልፅ የሚያንፀባርቁ ፣ ሲሻቸው አገር መበታተን እንደሚችሉ በህግ የተፈቀደላቸው ሀይሎች ባንዲራ እያወለበለቡ ነው። ህወሀት ባንዲራ አለው – የህወሀት ባንዲራ ከትግራይ እና ከኢትዮጵያ ህዝብ ታሪክ እና ማህበራዊ ግንኙነት አንፃር ለማንኛውም ሰው ግልፅ ሆኖ የሚታይ መግለጫ የለውም። ህወሀት ግን ባንዲራ አስፈልጎት ነበር – ኢትዮጵያን ከባዕድ ጠላት ለመታደግ ሳይሆን ይልቁንም የኤርትራን መገንጠል ለማቀላጠፍ ፣ የሌሎችንም ግንጠላ ለማመቻቸት – ህወሀት በቀሰቀሰው እርስ በርስ ውጊያ የተጠቁት ሁሉም ኢትዮጵያውያን ናቸው – ኢትዮጵያ አንድነቷ ይጠበቅ ያሉ ወገኖች ደም ነው የፈሰሰው።
እናም ኢትዮጵያን ወደብ አልባ አድርጎ ማስቀረት ብቻ ሳይሆን የመኖር ዋስትናዋ እንዲዋዥቅ የሚያረጋግጥ ባንዲራ በየመንደሩ በግዴታ እየተውለበለበ ነው። በየመንደሩ የተሰቀለውን የተጠቃቀመ ጨርቅ ከነ ግሳንግሱ ጥላቻ እና ቂሙ ጋር ሙዚየም ማውረድ የዚህ ትውልድ ሀላፊነት ነው። ጥላቻ እና አለመታማመን ብሎም ዘረኝነት በየመንደሩ ተክሎ ስለ ብሔራዊ ኩራት እና ታሪክ ማውራት አይቻልምና!
እርግጥ ነው ከብሔራዊ ባንዲራ ሌላ ክፍለ አገራት ወይንም የግዛት ክልሎች የራሳቸውን ሰነደቅ አላማ እንደ አስፈላጊነቱ ይቀርፃሉ። በተግባር እንደምናየው በሰለጠነው አለም ሳይቀር ክፍለ አገራት የክልላቸውን ታሪዊ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ እውነት የሚያንፀባርቅ ባንዲራ ያውለበልባሉ። ለምሳሌ ካናዳ እያንዳንዱ ክፍለ አገር ከብሔራዊ ባንዲራ ዝቅ ብሎ የሚሰቀል የራሱ ባንዲራ አለው – በዘር ላይ የተመረኮዘ ሳይሆን ባንድ ታሪካዊ አጋጣሚ በተሰመረ ድንበር ክልል ያለውን ልዩ ልዩ ባህል እነ ቋንቋ ተናጋሪ የሆነ ዜጋ የሚያንፀባርቅ። በአለም ላይ የዘር ባንዲራ በህግ ተገዶ የሚውለበለብባት አገር የወያኔይቱ ኢትዮጵያ ብቻ ናት። የትግራይ ፣ የኦሮሞ ፣ የአማራ ፣ የቤንሻንጉል… ባንዲራ ተብሎ ዘረኝነት ፣ ጥላቻ ፣ ቂም በየመንደሩ እየተነሰነሰ ነው። ትናንት ለኢትዮጵያዊነት ህልውና መረጋገጥ ህይወታቸውን የሰዉ የሁሉም ክልል ዜጎች ክቡር መስዋዕትነታቸውን የሚመሰክረው አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ ተፍቋል ፣ ኮስምኗል – ተደልዟል!!
‘በባንዲራ አምላክ’ ብሎ ጥቃት የመጣበት ዜጋ ሁሉ አጥቂውን መገዘት ማስቆም ይችል እንደነበር እናውቃለን – ይህም ባንዲራ እንደ በላይ ህግ እና አገራዊ ክብር መግለጫ መሆኑን ያመለክታል። በክብር ተይዞ የቆየውን ባንዲራ ጨርቅ ብቻ መሆኑን ያስገነዘበን ሟቹ ዘረኛ ጠቅላይ ሚኒስትር ያንን ታሪካዊ ባንዲራ ይበልጥ ለማራከስ ሲል ከለከት ቢስ ቃላት ባሻገር በዘር ላይ የተመረኮዙ አስራ ሁለት የዘር ባንዲራዎች አስታቅፎናል – ከየመንደሩ የመለመላቸው ባንዳዎች ጨርቁን ጠቃቅመው ሰቅለዋል። አውርዶ ወደሙዚየም መላክ የዚህ ትውልድ ሀላፊነት ነው። በህግ የበላይነት ላይ የታነፀች ፣ በታሪኳ የምትኮራ አገር መሰርቶ ማለፍ የዚህ ትውልድ ሀላፊነት ነው።
የዛሬ ሀያ አራት ዓመት የዲሞክረሲ ዝንጣፊ በወያኔ አንቀልባ ታዝሎ የመጣልን መሆኑም ተነገረን – የነፃ ሀሳብ ፣ የነፃ ምርጫ ተስፋ ፣ እኩልነት ፣ የነፃ መደራጀት ፍላጎት ፣ የነፃ ሰለፍ መውጣት… ሁሉም ፖለቲካዊ ጥያቄ በነፃ ይፈታል ሲሉ ነገሩን – መገንጠል እንኳ ነፃነት መሆኑን አረዱን። ውሎ ሳያድር ብሶቱን ለመግለፅ አደባባይ የወጣን ዜጋ ‘… ክልደከመው ባንዲራውን ቀስሮ ሲዞር ይዋል…’ ሲል መለስ ዜናዊ አላገጠ። ዲሞክረሲ የሚባል ነገር ከቶውንም እንደሌለ ጆሮ ላለው ሁሉ ይፋ አደረገ።
ስልጣን በያዙ ሰሞን አያያዙን አላልተው ሲያይ መብት የተጎናፀፈ የመስለው ዜጋ የመሰረት ድንጋዩ ቀስ በቀስ እየተመዘዘ እንደተቦረቦረ ሲመጣ ጫጫታ ብናበዛ ትርፉ… ግመሎቹ ይጓዛሉ አይነት አደንቋሪ የወያኔ ትዝብት ላይ መውደቅ ነው። ዲሞክረሲ ስሙ ሸጋ ነው – ስለሆነም በሚያምር ፣ በሚያማልል ስሙ ለመጠራት ወያኔን ጨምሮ የማይመኝ የፖለቲካ ሀይል በምድር ላይ አለ ማለት አይቻልም።
ልጅ እግር ዲሞክረሲ ፣ ወጣት ዲሞክረሲ ፣ ጎምቱ ዲሞክረሲ ፣ ሰሞኑን አንድ ሀተታ የለጠፈ የወያኔ ሹም ደግሞ አምሰት መቶ ዓይነት ዲሞክረሲ እንዳለ ነግሮናል። በአለም ላይ ያሉ አገሮች አምስት መቶ አይሆኑም እንጂ የትኛው የት አገር የቱ እንደተሰራበት ንገረን ብለን በጠየቅነው። ይኼ ሁሉ ግን ወያኔ መደበቂያ ፍለጋ ሲል የዲሞክረሲን መሰረታዊ እሴቶች ለማድበስበስ የሚጠቀምበት የድንቁርና አካሄድ ነው ከማለት ሌላ ማለት አይቻልም። አምስት መቶ ዓይነት ዲሞክረሲ አለ ማለት አንዱን ተግባር ላይ እያዋልን ነን ለሚል ቅጥፈት ያመቻቻል። ለዲሞክረሲ ያለተፈጥሮው ስም ያወጡለታል – መምሰል እና ሆኖ መገኘት ለየቅል መሆኑን ዘንግተው ያምታታሉ። በመሰረቱ አንድ ነገር ወጣት ነው ሲባል ትርጉሙ ትኩስ ጉልበት ያለው ፣ ሮጦ የማይደክመው ፣ ለማወቅ ለመማር ያለው ፍላጎት የገዘፈ ፣ ሙሉ ሀይሉን ተጠቅሞ በሁሉም መስክ ስኬት ለማስመዝገብ የማይታክት ማለት ነው።
ወጣት ዲሞክረሲ?
ወጣት ማለት ከቁመና ማማር ጀምሮ በሚያፈልቃቸው ጥያቄዎች ልክ መልስ ለማግኘት የማይታክት ነው። ታዲያ ዲሞክረሲው ወጣት ነው ካልን ልፍስፍስ ፣ ውሽልሽል ፣ ግራ የተጋባ ፣ ቁርጠኝነት የሚጎድለው ለውድቀቱ ሁሉ ሌሎችን የሚከስ ፣ አስመሳይ እና የመድረክ ተዋናይ እዩኝ ባይ አይነት ብቻ ሲሆን እንዴት ሆኖ ዲሞክራሲያዊ ይሰኛል?… ዲሞክረሲ እና የህግ የበላይነት የማይነጣጠሉ ያንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች መሆናቸውንስ ማን ይዘነገዋል? በዚህስ ተዘናግቶ ራስን ማታለል እሰከመቼ ይቀጥላል?
ዲሞክረሲ ዕለት-ተለት የሚኖሩት ማህበራዊ አደረጃጀት ብቻ ሳይሆን ዳይናሚክ በሆነ የማያቋርጥ እንቅስቃሴ ሂደት ለዜጎች ሰብአዊ ክብር መረጋገጥ እና የተሻለ አኗኗር መስፈን ተስፋ የሚዘራ የዕድገት መደላደል ነው። ካንዱ ዘመን ወደ ሚቀጥለው ሲሸጋገር ዜጋው በህግ ጥላ ስር ሙሉ መብቱ ይበልጥ እየተረጋገጠ መሄዱን ፣ ሰብአዊ ክብር ተፈጥሯዊ ፀጋ እንጂ ጉልበተኛ ሹም እንደ ራስ ምታት መድሀኒት እየመጠነ የሚሰጠው ኪኒን አለመሆኑን የሚያመለክት ማሳያ መስተዋት ነው… ዲሞክረሲ የሚዳብረውም ሆነ የሚጎለብተው ግን መጀመሪያ ህልውና ሲኖረው ብቻ ነው።
ዲሞክረሲ ጭብጥ ነው። ጭብጥ ሆኖ ካልዳሰሱት ፣ ካላዩት ፣ ካልኖሩት እንደ መንፈስ እንደ ትንተና ዘዴ በፖለቲከኞች ምላስ ብቻ የሚንበለበል ቀመር አይደለም።ዲሞክረሲ ህልውና እንዲኖረው ፖለቲካዊ ብስለት ብቻ ሳይሆን ፖለቲካ ቁርጠኝነትም ይጠይቃል – ስለሆነም ዲሞክረሲ በተጨባጭ የህግ የበላይነት ማለት ነው – ማንም ከህግ በላይ አለመሆኑ የተረጋገጠበት ህብረተሰብ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ሊባል ይችላል – ይህ በሌለበት ቦታ ግን ዲሞክረሲ የለም – ከሌለ ደግሞ የለም።
በህግ ጥላ ስር መኖር ለተረጋጋ ማህበራዊ ህይወት መሰረት ነው። የሀሞራቢ ህግ አይን ያጠፋ አይኑ ይጠፋል ሲል – ማንም ይሁን ማን በዚያ ግዛት ክልል ነዋሪ የሆነ ዜጋ ሁሉ የዚህ ህግ ተገዢ ይሆናል ማለት ነው – ከዚህ አንፃር ህግ የሰፈነበት ህብረተሰብ ነበር ማለት ያስደፍራል። አይን አጥፍቶ አይኑ ያልጠፋ ሰው በሀሞራቢ ዘመን ከተገኘ የፍርድ መጓደል ተከስቷል ማለት እንጂ እንዴት አይነት ጨካኝ ህግ ነው? የሚል ትችት ሊቀርብ አይችልም። 
የሀሞራቢ መንግስት አይን ካላጠፋህ አይንህን አያጠፋም – አሸባሪ ሳትሆን ስም አይለጥፍብህም። መገንጠል መብት ነው ብሎ በደማቅ ብዕር ህግ ያወጣ የፖለቲካ ሀይል ያንን ህግ መልሶ ከረገጠ ለህገወጥነት መንሰራፋት ትልቁ ማሳያ ነው። ራሱ ደንግጎ ያወጣውን ህግ የሚረግጥ ህግ አውጪ እና አስፈፃሚ መንግስት ዞር ብሎ በህግ እየገዛሁ ነው ማለት አይችልምና። ያን አይነቱ መንግስት የወሮበላ መንግሰት ይባላል። ወሮበሎች ከተደራጁ እና በበቂ ከታጠቁ የመንግሰት ስልጣን መቀማት ይችላሉ… የሚከተለው ምን እንደሆነ ግን የወያኔ አስተዳደር በቂ ማሳያ ነው። ሲፈልግ ያስርሀል ፣ ስም ያወጣልሀል… አሸባሪ ቂብጢርሶ ይልሀል – ደግሞ በል ሲለው ነፃ ነህ ብሎ ከወህኒ ይለቀሀል – የቱጋ ነው ህግ የተከበረው? እስከመቼስ ነው ሲሻቸው እንደበግ ጎትተው ሲያስሩ ሲፈቱን የሚቆዩት – እስከመቼስ ነው የዘረኞች ባንዲራ በየመንደሩ ሲነሰነስ የምናየው?
በድንጋይ ዳቦ ዘመን ተፈጥሯዊ የስራ ክፍፍል ከመኖሩ በስተቀር የሰው ልጅ መዋቅራዊ አስተዳደር ለመዘርጋት የቻለበት ደረጃ ላይ አልነበረም። ሰው ይኖር የነበረው ለመብላት – የሚበላውም ለመኖር ነበር።
ለምግብ ዋስትና ሲባል መባላት ያኔ ጥንት ጭምር የነበረ መሆኑን ማንሳቱ ተገቢ የሆነበት ዘመን ላይ ነን። ሰው እየበላ ደግሞ እየተባላ ወዲህም እያሰበ እየተሳሰበ – ደግሞ እየበላ ህልውናውን አቆይቷል። ዛሬ ዛሬ ደግሞ ነገሩ ተሻሽሏል – ቀለቡንም ተቀላቢውንም ለመቆጣጠር ነፃ አውጪ ሰራዊት ማሰለፍ። ተጋድሎ ተሟሙቶ መሬት መቆጣጠር ማስገበር – የገበረ ህዝብ ምርኮ ነው – አስገባሪው እንደፈቀደ ያሳድረዋል። ምርኮኛ ህዝብ የሚያዝበት ንብረት የለውም – ከመሬቱ ቢያፈናቅሉት ፣ ከአገር ቢያሰድዱት… ባንዲራውን እንኳ ቀምተው የነሱን ዘረኛ ባንዲራ ያውም የተወጋበትን ፣ በቁሙ የተዋረደበትን ፣ እና የተበደለበትን እንዲያወለበልብ ቢያስገድዱት ምርጫ የለውም – ልጆቹ ለብሔራዊ ክብሩ እና ነፃነቱ መረጋገጥ በፍልሚያ የወደቁለትን ባንዲራ ቀምተው የነሱን ዘረኛ የቂም እና በቀል ባንዲራ ያስታቅፉታል።
በደቡብ ካሮላይና የተጀመረው የዘረኞችን ባንዲራ ወደ ሙዚየም የመላክ እርምጃ ተከትለን ዘር እና ጎጥ ቆጥረው የተደራጁ የዚህ ዘመን ደናቁርት የተከሉብንን የጥፋት ባንዲራ ፈጥነን እናውርድ – ወደ ተፈጥሯዊ ቤቱ ወደ ሙዚየም እንላከው!!

Comments

Popular posts from this blog

Addis standard’s exclusive interview with Ana Gomes