የኢትዮዽያ ተቃዋሚዎች እንደ ዳይኖሰር ከምድረ ገፅ ከመጥፋት ይዳኑ።


ዚምባብዌ ውስጥ ነው አሉ – በአዛውንቱ የሙጋቤ አገር፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ በጥባጭ (Rogue) ዝሆኖች ከተፈቀደላቸው የመኖርያ ክልል በመውጣት የነዋሪዎችን ማሳና ጎጆ እየደረማመሱት ይሄዱ ጀመር። በፖለቲካ ቋንቋ “ነውጠኛ” ሆኑ ማለት ነው- ዝሆኖቹ፡፡ የዚምባቡዌ መንግስት ደግሞ ለ“ነውጠኛ ተቃዋሚዎች” እንጂ ለነውጠኛ ዝሆኖች ምላሽ ሰጥቶ አያውቅም፡፡ እናም ትንሽ ታገሳቸው። ዝሆኖቹ ግን መደረማመሱ ተመቻቸው መሰለኝ ደጋግመው ወደ ገበሬዎቹ ማሳ በመመላለስ የከፋ ውድመት አደረሱ፡፡
ይሄኔ መንግስት በነውጠኛ ተቃዋሚዎች ላይ መውሰድ የለመደውን እርምጃ ሊወስድባቸው የጦር መሳሪያውን መወልወል ጀመረ – ቃታ ሊስብ፡፡ የማታ ማታ ግን አማካሪ አይጥፋ ሃሳቡን ቀየረ፡፡ እርምጃው በዓለም አቀፍ የዱር እንስሳት መብት ተሟጋቾች ዘንድ መብጠልጠልንና መወንጀልን ስለሚያስከትል ሌላ መላ ተዘየደ – በአማካሪዎቹ ሃሳብ አመንጭነት። እናም የዚምባብዌ መንግስት በተለያዩ ድረ-ገፆችና ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ተከታዩን መልእክት አሰራጨ፡-
“በመላው ዓለም ለዱር እንስሳት መብት ተሟጋች ነን የምትሉ ወገኖች ሁሉ፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዱርዬ ዝሆኖች ከመኖሪያቸው ክልል ወጥተው የህብረተሰቡን ህይወት እየረበሹ ነውና… በፍጥነት ደርሳችሁ በራሳችሁ ትራንስፖርት ሰብስባችሁ በመውሰድ ለምትፈልጉት ጉዳይ (ለሰርከስ ይሁን ለሌላ) መጠቀም እንደምትችሉ እያሳወቅን፤ ይሄን በአስቸኳይ ባታደርጉ ግን በዝሆኖቹ ላይ የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ እንደምንገደድ እንገልፃለን”
መረጃው በተሰራጨ 24 ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከዱር እንስሳት መብት ተሟጋች ድርጅቶች አንዱ በፈጣን አውሮፕላን ዚምባብዌ ገጭ አለ። ወዲያው ከመንግስት ጋር ተደራድሮ ዝሆኖቹን ሰበሰበ፡፡ እድሜ ለመብት ተሟጋቾች! የዚምባብዌ ዝሆኖች “ነውጠኛ” በሚል ተፈርጀው በጅምላ ከመረሸን ተረፉ፡፡ የበለጠ ከሚያውቃቸው የአፍሪካ መንግስት ይልቅ በዱር እንስሳትነታቸው (በመንፈስ እንደማለት ነው) ብቻ የሚያውቃቸው ምዕራባዊ የመብት ተሟጋች ድርጅት ህይወታቸውን ታደጋቸው፡፡ ለነውጠኞቹ ዝሆኖች  ተወልውሎ የነበረው የጦር መሳሪያ ለተቃዋሚዎች (ለስልጣን ተቀናቃኞች ማለት ነው!) ተብሎ ተቀመጠ። (ለማስፈራርያ እኮ ነው!)
ከላይ የቀረበውን ታሪክ ያወጋኝ አንድ የቅርብ ወዳጄ ነው – አነበብኩት ብሎ፡፡ እኔ ታዲያ ወዲያው አንድ  ሃሳብ ብልጭ አለልኝ፡፡ ዶሮ ብታልም ጥሬዋን እንዲሉ… ዝሆኖቹ ከጅምላ ጭፍጨፋ የዳኑበትን ምስጢር  ለኢትዮዽያ ተቃዋሚዎች ለምን አንጠቀምበትም አልኩኝ – ለራሴ፡፡ ትንሽ በውስጤ ካብሰለሰልኩት በኋላ ግን ይኸው ለናንተም አቀረብኩት፡፡ በዝሆኖቹ ታሪክ ኢንስፓየር ሆኜ ያመነጨሁትን አዲስ ሃሳብ!!  ለኢትዮዽያ መንግስት ከረባሽ ዝሆኖችና ከተቃዋሚዎች የቱን ትመርጣለህ የሚል ጥያቄ ቢቀርብለት፣ ረባሽ ዝሆኖችን እንደሚመርጥ ሳይታለም የተፈታ ነው። (ስልጣን መነቅነቅና ማሳ መደርመስን ምን አገናኛቸው?!)
እናንተ ስለኢትዮዽያ መንግስታት ያላችሁን ግንዛቤ በትክክል ባላውቅም እኔ ግን በአንድ ነገር እርግጠኛ ነኝ፡፡ የኢትዮዽያ መንግስታት በምዕራባውያን የኢኮኖሚ ተፅዕኖ ስር ባይሆኑ ኖሮ፣ እስካሁን ተቃዋሚዎች እንደ ዳይኖሰር ከምድረ ገፅ መጥፋታቸው አይቀርም ነበር፡፡ ከተቃዋሚዎች ቀጥሎ እንደ ዳይኖሰር የሚጠፋው ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? “ምርጫ” የሚለው ቃል ነው። ይሄን ቃል ተከታትለው ከኢትዮዽያ ምድር የሚጠፉት “ዲሞክራሲ” እና “የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት” የሚሉ ቃላትና ሃረጎች እንደሚሆኑ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡
ወደ ዋና ጉዳያችን ስንመለስ … ለኢትዮዽያ ተቃዋሚዎች ብዬ ያመነጨሁት ሃሳብ ለኢትዮዽያ መንግስታትም በእጅጉ የሚበጅ መሆኑን አስረግጬ እናገራለሁ፡፡ በነገራችሁ ላይ በአብዛኞቹ የመንግስት  ተቃዋሚዎች በገዢው ፓርቲ ላይ የሚነሱትና “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” ብለው ህብረት የሚፈጥሩት በምርጫ ዋዜማ ነው፡፡ ያኔ መንግስት ጠባይ ያለውን ሰብስቦ ወህኒ ያጉራል። ትዕቢት ትዕቢት የሚለው ካለ ደግሞ ጥርሱን ሊያወልቀው ይችላል፡፡
እኔ የምለው…ባለፈው ሳምንት የአንድነት አመራር አባልን ጥርስ ያወለቁት የደህንነት ኃይሎች ናቸው የተባለው እውነት ነው እንዴ? (ጥያቄ ነው!) ከመንግስት ወገን ማረጋገጫ አልተሰጠም ብዬ እኮ ነው (መች ተሰጥቶ ያውቃል እንዳትሉኝ!) ባለፈው ምርጫ የኢህአዴግ ካድሬዎች የአንድነትን የቅስቀሳ መኪና ጐማ አተነፈሱ ተብለው መወንጀላቸውን ሰምቼ ነበር። ከራሳቸው ከአንድነቶች፡፡ ነገርዬው ተገቢ ባይሆንም ጥርስ ከማውለቅ ግን ሺህ ጊዜ ይሻላል፡፡ (ማውለቅም ማተንፈስም ቢከለከል ጥሩ ነው!)
እናላችሁ —- የባሰባቸው  መንግስታት ዓይን ከማጥፋትም ወደ ኋላ አይሉም (ምን ነካችሁ— ነገርዬው ሥልጣን እኮ ነው!) ይሄ ደግሞ ምዕራባውያኑ  ጆሮ መድረሱ አይቀርም፡፡፡ የኢትዮዽያ መንግስታት እቺን እቺን ፈፅሞ አይፈልጓትም፡፡ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ነን ባዮች ሪፖርትም ይከተላል፡፡ ከዚህ ሁሉ ጣጣ ያድናል ባይ ነኝ አዲሱ የመፍትሄ ሃሳቤ፡፡ እናላችሁ… የኢትዮዽያ መንግስት በምርጫ ዋዜማ ላይ ልክ ለረባሾቹ ዝሆኖች ያሰራጩት አይነት መልእክት በተለያዩ ሚዲያዎች ያሰራጫሉ – ለሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፡፡ እንዲህ ሊል ይችላል፤ መልእክቱ -
“በመላው ዓለም የሰብአዊ መብት ተሟጋች ነን የምትሉ ወገኖች ሁሉ፤ በዚህች አገር ላይ የሚገኙ ነውጠኛ ተቃዋሚዎችን በራሳችሁ ትራስፖርት ሰብስባችሁ በመውሰድ (ለሰርከስ ይሁን ለሌላ) ለምትፈልጉት ጉዳይ መጠቀም የምትችሉ መሆኑን እያሳወቅን፣ ይህን የማታደርጉ ከሆነ ግን በነውጠኞቹ ተቃሚዎች ላይ ተገቢ ያልነውን እርምጃ ለመውሰድ እንገደዳለን”
ይሄ ማሳሰቢያ በተሰራጨ በአጭር ጊዜ ውስጥ እነ አምነስቲና ሂዩማን ራይትስዎች በፍጥነት ደርሰው የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትንና ደጋፊዎችን ሰብስበው ከአጥፊነትም ከመጥፋትም ይታደጓቸዋል – እንደ ረባሾቹ ዝሆኖች ማለት ነው፡፡
በዚህም የኢትዮዽያ ተቃዋሚዎች እንደ ዳይኖሰር ከምድረ ገፅ ከመጥፋት ይድናሉ – በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጠባቂነት፡፡ የኢትዮዽያ መንግስትም በአምስት ዓመቱ ለምእራባውያን እርዳታ ሲሉ  ሲያደርጉት ከነበረው የይስሙላ ምርጫ ይገላገላሉ። (እፎይ ብለው የሰላም እንቅልፍ ይለጥጣሉ!) በሆነ ተዓምር ተቃዋሚዎች ከስልጣን ነቅንቀው ይጥሉን ይሆን? ከሚል ራስ ምታት ይገላገላሉ፡፡ (Win/Win Situation ይሏል ይሄ ነው!)
ወዳጆቼ፤ሌላው ሁሉ መፍትሔ ተሞክሮ ስላልሰራ ይሄ ደሞ ይሞከራ!! ተቃዋሚዎችን ከመጥፋት እንታደጋቸው፡፡
http://freedom4ethiopian.wordpress.com/2014/07/12/7h/

Comments

Popular posts from this blog

Addis standard’s exclusive interview with Ana Gomes